28 September 2018 Written by 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 1204 ሰዎችን አስሮ የማነፅ /የማረም/ ስልጣን አለው ወይ? ሕጋዊነቱስ ምን ይመስላል?

 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን በሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ 28 ሰዎች መሞታቸውን፣ በፖሊስ ከተያዙ ሰዎች መካከል በርካቶች በምክር መለቀቀቃቸውን፣ 174 ሰዎች በሕግ አግባብ በፍርድ ሒደት ተጠያቂ እንደሚሆኑ እንዲሁም 1204 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ሠንዳፋ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ለማነፅና ወደፊት ሲታረሙ ወደ ሕብረተሰቡ ለመቀላቀል ሲባል ጦላይ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚቆዩ በይፋ ተገልጿል፡፡

ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት ወንጀልን መከላከልና ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ የወንጀል ምርመራ የማጣራት፣ ተጠርተሪዎችን በሕግ አግባብ የማሰር፣ የታሰሩትን ሰዎች ፍርድ ቤት በማቅረብ እንደ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈፀም ሕጋዊ እና ዋነኛ የፖሊስ ሥራ ከመሆኑ በተጨማሪ የፖሊስ ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ፖሊስ ዜጎችን ከጥቃትና ከወንጀል የሚከላከል የዜጎች ከለላ እንጂ ለዜጎች ስጋት የሚሆን የመንግስት አካል አይደለም፡፡ ዜጎችም ፖሊስን ሲያዩና ስለ ፖሊስ ሲሰሙ ሊሰማቸው የሚገባው ደህንነትና ምቾት ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ፖሊስም ሕግ በማክበርና በማስከበር እንዲሁም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ በኩል ምሳሌ ሊሆን የሚገባው ግንባር ቀደም ተቋም ነው፡፡

ፖሊስ ወንጀልን መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ ማጣርት፣ በወንጀል ጠርጥሮ የተለያዩ ተጠርጣሪዎችን ማሰር፣ የታሰሩ ሰዎችን በፍርድ ቤት አቅርቦ ያሰረበትን ምክንያት በመግለፅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ፣ በፍርድ ቤት ዋስትና ሲፈቀድ ያሰራቸውን ተጠርጣሪዎች መፍታት፣ የተጠናቀቁ የወንጀል ምርመራ መዛግብትን ለዐቃቤ በማቅረብ ሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ ማሰጠት እና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት በሕግ በግልፅ የተመለከቱና የዕለት ተዕለት የፖሊስ ተግባራት ናቸው፡፡

በዚሁ አግባብ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ከሰሞኑ ከያዛቸውና በምክር ከተለቀቁት እንዲሁም በሕጋዊው የፍርድ ሒደት ይጠየቃሉ ከተባሉት 174 ሰዎች ውጪ ያሉትን 1204 ሰዎችን አስሮ ቀደም ሲል በሰንዳፋ በመቀጠልም በጦላይ እንዲታነፁና እንዲታረሙ አድርጌ ከሕብረተሠቡ እቀላቅላለሁ ማለቱ ሕጋዊነቱ ምን ይመስላል? ኮሚሽኑስ ይኼን የማድረግ ሥልጣን አለው ወይ? የሚሉትን በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡

የዚሀ ጽሑፍ ዓላማም በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ለምን ታሰሩ ለማለት ወይም ወንጀል አልተፈፀመም ለማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ላይ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባውን ሕጋዊ አካሄድና ሥርዓት ለፖሊስ ከተሰጠው ሥልጣን እንዲሁም በ1204ቱ የታሰሩት ሰዎች ላይ ከተተገበረው አካሄድ አንፃር መመርመር ነው፡፡

ፖሊስ ከ1204ቱ ሰዎች እስር እና አቆያየት ጋር በተያያዘ ሊፈፅማቸው ይገባ የነበሩ ሕጋዊ ተግባራት ምንድን ናቸው?

ፖሊስ 1204ቱን ሰዎች ከወንጀል ጋር በተያያዘ ጠርጥሮ ካሰረ የሚከተሉትን ኃላፊነቶች የመወጣት ሕጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ እነዚህም፡ -

የታሰሩትን ሰዎች በ48 /አርባ ስምንት ሠዓታት/ ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ፤

የታሰሩትን ሰዎች በምን ምክንያት እንዳሰረ ለፍርድ ቤት የማስረዳት ግዴታ፤

ፖሊስ በወንጀል ጠርጥሮ ያሰራቸውን ሰዎች በ48 ሠዓታት ፍርድ ቤት ካቀረበና ያሰረበትን ምክንያት ካስረዳ በኋላ ለተጨማሪ ጊዜ ተጠርጣሪዎቹን በእስር ማቆየት ከፈለገ ፍርድ ቤቱ ከ14 ቀናት ላልበለጠ ተጨማሪ ጊዜ ተጠረጣሪዎቹን አስሮ ማቆየት እንዲችል ፍርድ ቤት የማስፈቀድ ግዴታ አለበት፤

ፍርድ ቤት ለተጨማሪ ጊዜ ተጠርጣሪዎቹ በእርስ ሊቆዩ አይገባም ብሎ ዋስትና ከፈቀደ ፖሊስ ተጠረጣሪዎቹን ከእስር የመልቀቅ ግዴታ አለበት፤

የወንጀል ምርመራ ተጣርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ በምርመራ መዝገቡ ላይ ሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ እንዲሰጥበት መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ የማቅረብና የማወሰን ግዴታ አለበት፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀፅ 17 /2/ መሠረትም ማንኛውም ሠው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር እንደማይችል ተመልክቷል፡፡

ሆኖም 1204ቱ ሰዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ሳያቀርብባቸው እና በፍርድ ቤትም ጥፋተኛ መሆናቸውን በፍርድ ሳይረጋገጥ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ጥፋተኛ /ወንጀለኛ/ ናቸው ብሎ ስላመነ በጦላይ እንዲታረሙ እየተደረገ ነው፡፡

ፖሊስም 1204ቱን ሰዎች በተመለከተ ተጠራጣሪዎቹን ባሰረ በ48 /አርባ ስምንት/ ሠዓታት ፍርድ ቤት ውስጥ ሳያቀርብ፣ ተጠረጣሪዎቹን ያሰረበትን ምክንያት ለፍርድ ቤት ሳያስረዳ፣ ለተጨማሪ ቀናት ተጠርጣሪዎቹን በእስር አቆይቶ ምርመራ ለመቀጠል ፍርድ ቤትን ሳያስፈቅድ፣ የምርመራ መዛግብት ላይ በዓቃቤ ሕግ ክስ ሳይመሰረትና ፍርድ ቤትም የተጠረጣሪዎችን ጥፋተኛነት በማስረጃ አጣርቶ ሳያረጋግጥ ፖሊስ ተጠርጣዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ እንደወንጀለኛ በመቁጠርና ሊታረሙ እንደሚገባ ድምዳሜ ላይ በመድረስ ተጠርጣሪዎቹን አርማለሁ /አንፃለሁ/ ማለቱ ሀገሪቱ ያፀደቀቻቸውን ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች፣ ሕገ መንግስቱን እንዲሁም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉንና ሌሎች ሕጎችን የሚጥስ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በወንጀል ጠርጥሮ የያዛቸውን ሰዎች የማረም /የማነፅ/ ሕጋዊ ሥልጣን አለው ወይ?

ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥልጣንና ኃላፊነትን የሚሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 96/1996 አንቀፅ 6 ነው፡፡ ድንጋጌው የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ ማጣራትን ጨምሮ 14 /አስራ አራት/ ሥልጣንና ተግባራትን ለኮሚሽኑ የሚሰጥ ቢሆንም ኮሚሽኑ በወንጀል ጠርጥሮ ያሰራቸውን ሰዎች የማነፅና የማረም ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸውን ሰዎች የማረምና የማነፅ ሥልጣንም በአዋጅ ቁጥር 365/1995 የተሰጠው ለፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ብቻ ነው፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ በወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ የያዛቸውን ሰዎች በማረምና በማነፅ ከሕብረተሰቡ እቀላቅላቸዋለሁ ያላቸውን 1204 ሰዎች የማረምም ሆነ የማነፅ ሕጋዊ ሥልጣን የለውም፡፡

በእስር ላይ የሚገኙት 1204 ሰዎች የተጣሱባቸው መብቶች ምንድን ናቸው?

በተያዙ በ48 /አርባ ስምንት/ ሠዓት ውስጥ ፍ/ቤት የመቅረብ መብታቸው /የሕገመንግስቱ አንቀፅ 19/3/ እና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 29/2/፤

በዋስትና የመለቀቅ መብት፤ /የሕገመንግስቱ አንቀፅ 19/5/ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 28 እና 64/

የነፃነት መብት /የሕገመንግስቱ አንቀፅ 17/1/

በሕገ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ያለመያዝ፣

ክስ ሳይቀርብ ወይም ፍርድ ሳይሰጥ ያለመታሰር መብት /የሕገመንግስቱ አንቀፅ 17/2/

በሕግ አግባብ ክስ ቀርቦባቸው በፍርድ ቤት ቢዳኙ ኖሮ ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸውን ግልፅ በሆነ ችሎት የመስማት፤ ክሱ በቂና ዝርዝር ሆኖ እንዲነገራቸውና በፅሁፍ የማግኘት መብት፤ የሚቀርቡባቸውን ማስረጃዎች የመመልከትና የመጠየቅ መብት፤ የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብ መብት፤ በጠበቃ የመወከል መብት፤ ይግባኝ የማለት መብትና ሌሎች መብቶቻቸው ተጥሰዋል፡፡ /የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 20/

ከሕግ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙትን 1204 ሰዎች መብት የማስከበርና የማክበር ኃላፊነት የማን ነው?

1. የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

ኮሚሽኑ በሕግ መሰረት የተቋቋመ አስፈፃሚ አካል እንደመሆኑ መጠን ስራዎቹን ሊያከናውን የሚገባው በሕግ መሰረት ተለይቶ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት ነው፡፡

በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ ሀገሪቱ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብቶች የማክበር፣ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት ላይ ያሉና በሕገ መንግስቱ ላይ በግልፅ የተመለከቱ የተያዙ ሰዎችን መብቶች ማክበር እንዲሁም ኮሚሽኑ በደንብ ቁጥር 96/1996 አንቀፅ 6 ብቻ ተለይተውና ተቆርጠው የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባራት ብቻ በማከናወን በእስር ላይ የሚገኙትን 1204 ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ማድረግ ወይም በተጨባጭ በምርመራ የተረጋገጠ ወንጀል ካለ ዐቃቤ ሕግ በምርመራ መዝገብ ላይ ሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ እንዲሁም የተያዙት ሰዎች መያዛቸው እንዲታወቅ ለፍ/ቤት ማቅረብና የፍ/ቤትን ትዕዛዝ መጠባበቅ ይጠበቅበታል፡፡

2. የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑ በደንብ ቁጥር 96/1996 አንቀፅ 3 /2/ እና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 አንቀፅ 20 /1/ ተመልቷል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዓመታዊ የስራ ዕቅድና የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትና የሚያቀርበው ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደመሆኑ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 1204 ሰዎች የተያዙበትንና ታስረው የሚገኙበትን አግባብ፣ ሕግ የሚከበርበትን እንዲሁም የተያዙት ሰዎች መሠረታዊ መብቶች የሚከበርበትን ሁኔታ የመከታተልና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

3. የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ 6 ስር ከተሰጡት በርካታ ሥልጣንና ተግባራት መካከል የወንጅል ምርመራ በሕግ መሰረት መከናወኑን የማረጋገጥና አስፈላጊ ትዕዛዝ የመስጠት፣ የተጀመረ የወንጀል ምርመራ በአግባቡ ተከናውኖ እንዲጠናቀቅ የማድረግ፣ የተጀመረ የወንጀል ምርመራ መጀመሩን የማወቅና ክትትል የማድረግ፤ ምርመራቸው የተጠናቀቁ የምርመራ መዛግብት ላይ ሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ የመስጠት፣ በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎችን የመጎብኘት አያያዛቸው እና ቆይታቸው በሕግ መሰረት መፈፀሙን የማረጋገጥ፤ ሕገወጥ ተግባር እንዲታረም የማድረግ እንዲሁም ሕግን ተላልፈዋል በተባሉ ሰዎች ላይ በሕግ መሰረት እርምጃ የመውሰድና እንዲወሰድ የማድረግ እንዲሁም ሀገሪቷ ያፀደቀቻቸውን ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስምምነቶችን አፈፃፀማቸው የመከታተልና ሌሎች ይገኙበታል፡፡

በዚሁ መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ 1204ቱ ሰዎች በምን ምክንያት እንደተያዙ የማጣራት፣ የወንጀል ምርመራ የተጀመረ መሆኑን የማረጋገጥ ምርመራውን በበላይነት የመምራት፣ ምርመራው ከተጠናቀቀ ተገቢውን ሕጋዊ አስተየያትና ውሳኔ የመስጠት፣ ተጠርጣሪዎቹ በተያዙ በ48 ሠዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውና ፍርድ ቤት ሳያውቀው በእስር ቆይተው ያለዐቃቤሕግ ክስና ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደጥፋተኛ ተቆጥረው እንዲታረሙ እየተደረገ ያለበት ሂደት ሕግን ያልተከተለና የታሳሪዎቹን ሰብዓዊ መብቶች የሚጥስ በመሆኑ ታሳሪዎቹን ከእስር እንዲለቀቁ በማድረግ ሕግን የተላለፉትን ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሕጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋምም የዜጎችን የሰብዓዊ መብቶች በማክበርና በማስከበር በኩል በርካታ ኃላፊነቶችና ተግባራትን እንዲወጣ በሕግ ኃላፊነት የተጣለበት እንደመሆኑ መጠን የ1204ቱን ሰዎች ጉዳይ በተመለከተ ተደራራቢ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል፡፡

4. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 210/1992 አንቀፅ 6 /1/ ከተጣሉበት ሥልጣንና ተግባራት መካከል በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች በማንኛውም ዜጋ፣ በመንግስት አካላት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሌሎች ማሕበራትና በባለሥልጣኖቻቸው መከበራቸውን የማረጋገጥና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመኖሩ በራሱ አነሳሽነት ጭምር ምርመራ ማካሄድ ይገኝበታል፡፡

በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ በቡራዩና አከባቢው ላይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጣርቶ ጥሰቶቹን በመለየት በመንግስት በኩል ሊስተካከሉና ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች እንዳሳወቀው ሁሉ በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ከተማ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስረው በጦላይ እንዲታረሙ እየተደረጉ ካሉ 1204 ሰዎች አያያዝና አቆያየት ጋር በተያያዘ የተፈፀሙና እየተፈፀሙ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቸን አጣርቶ የማስተካከያና የመፍትሔ እርምጃዎችን ለሚመለከታቸው አካላትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማሳወቅ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡

5. ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 74 /13/ መሠረት በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የዜጎችን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ፣ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 72 /1/ መሠረት ከፍተኛ የአስፈፃሚ አካል ሥልጣን የተሰጣቸው በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም በፌዴራል ፖሊስ በኩል ተጠሪነቱ ለእርሳቸው በመሆኑ እንዲሁም ሕግ የሚደነግገው እንደተጠበቀ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ “አጣርተን እናስራለን እንጂ አስረን አናጣራም” በሚል የገቡትን ቃል ሊያከብሩ ስለሚገባ ሳይጣራ መታሰር ብቻ ሳይሆን ዐቃቤ ሕግ ሳይከሳቸውና ፍርድ ቤትም ጥፋተኛ ሳይላቸው የታሰሩትንና ፖሊስ እራሱ መርመሪ፣ እራሱ ከሳሽ፣ እራሱ ፈራጅና እራሱ ፍርድ አስፈፃሚ በመሆን እየታረሙ ያሉትን 1204 ሰዎች እንዲለቀቁ ትዕዛዝ የመስጠትና ሕጋዊ ያልሆነውን እስር እየፈፀሙ ያሉ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ሕጋዊ ግዴታ ሊወጡ ይገባል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 77 /9/ መሠረት ሕግና ሥርዓት መከበሩን የማረጋገጥ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ዜጎችም በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊይዙ፣ ክስ ሳይቀርባበቸው ወይም ሳይፈርድባቸው ያለመታሰር መብትና ሌሎች በሕገ መንግስቱና ሌሎች ሕጎች የተረጋገጠባቸው መብቶች አሏቸው፡፡ የሚኒስተሮች ም/ቤትም እነዚህንና ሌሎች ሕጎች መከበራቸውን የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት በመሆኑ ሕግ ተጥሶ ያለአግባብ የታሰሩት 1204 ሰዎች የሚለቀቁበት ወይም በሕግ አግባብ ብቻ የሚጠየቁበት ሁኔታ ላይ ተገቢውን የማከናወን ኃላፊነት አለበት፡፡

6. የ1204ቱ ሰዎች ቤተሰቦችና ጠበቆች

የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ወይም ጠበቆች ፍርድ ቤት እንዲታሰሩና እንዲታረሙ ትዕዛዝ ወይም ፍርድ ሳይሰጥባቸው ከሕግ ውጭ ታሳሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆነው እንዲታረሙ በሚል ተገደው እንዳይዘዋወሩ የተከለከሉ፤ የተያዙ ወይም የታሰሩ መሆኑን በመግለፅ ያሰራቸው አካል በምን ምክንያት፣ በየትኛው ሕግና ስልጣኑ መሰረት እንዳሰራቸው ፍ/ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 177 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሰረት ክስ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡

የተለያዩ ሕጎችንና ሀገሪቱ የፈረመቻቸውንና የተቀበለቻቸውን የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች በሚጥስ መልኩ ያለ ዐቃቤ ህግ ክስና ያለ ፍርድ ቤት ፍርድ ፖሊስ ታሳሪዎችን አስሮና ጥፋተኛ ብሎ እያረመና እያነፀ መሆኑን በመግለፅ ከእስር እንዲለቀቁና ሕግ እንዲከበር የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ለራሱ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አቤቱታ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሕግ በተሠጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ከ1204ቱ ሰዎች ጋር በተያያዘ የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ካለ ምርመራውን በበላይነት እንዲመራ፣ ታስረው የሚገኙት ሰዎች የታሰሩበትን የሕግ አግባብ እንዲያጣራ፣ የታሰሩ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው በሕጋዊ መንገድ እንዲታይ ወይም ከእስር እንዲለቀቁ እንዲሁም ሕግ እንዲከበር አቤቱታ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ከታሠሩት ሰዎች አያያዝና አቆያየት አንፃር የሰብዓዊ መብቶች በፖሊስ በኩል የተከበሩና የተረጋገጡ ስለመሆን አለመሆኑ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ለሚመለከተው አካል እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ እንዲደረግ አቤቱታ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡

የአስፈፃሚ አካሉ ከፍተኛ የአስፈፃሚነት ሥልጣን ላላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሀገሪቱ ሕግ እንዲከበር ዜጎችም ሊታሠሩና ጥፋተኛ ሊባሉ የሚገባው የሕግ ሥርዓትን ብቻ በመከተል በመሆኑ ክስ ሳይቀርብና ፍርድ ሳይሰጥ ቅጣት እየተፈፀመ መሆኑ ሕጋዊ ስላልሆነ ተገቢው የማስተካከያና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ሊጠይቁ ይገባል፡፡

እንደ አጠቃላይ ያለአግባብ ታስረዋል የተባሉና ከእስር ሊፈቱ አይችሉም የተባሉ በርካታ ሰዎችን ከእስር ያስፈታ፣ ዜጎቹን ከውጭ ሀገራት ጭምር ከእስር አስፈትቶ ለሀገራቸው ያበቃ፣ በሀገሪቱ ይከናወናሉ ተብለው የማይታሰቡ በርካታ ተግባራትን ከፈፀመው የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ለሕግ የበላይነት ተገዢ በመሆን ከሕግ ውጪ ክስ ሳይቀርብባቸውና ፍርድ ሳይሰጥባቸው መርማሪውም፣ ከሳሹም፣ ፈራጁም ፍርድ አስፈፃሚውም ፖሊስ ብቻ ሆኖ ጦላይ በእስር ላይ ሆነው ቅጣት እየፈፀሙ ያሉትን 1204 ሰዎች እንዲለቀቁ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ብዙ ተስፋ ከተጣለበት መንግስትና ከለውጡ የምጠብቀውም ከቀደሙት የተሻለ ለሕግ ተገዢ የሆነ አስፈፃሚ አካል እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ በመሆኑ ራሱ መንግስት ሕግን እያከበረ ሕዝቡ ሕግ እንዲያከብር ምሳሌ ሊሆን ይገባል እላለሁ፡፡

Last modified on Friday, 28 September 2018 17:49
Abiyou Girma Tamirat

Abiyou Girma is a qualified and a licensed lawyer. He obtained Bachelor of Laws (LLB), his first degree, from Saint Marry's University, Faculty of Law, in June 2007 and master's degree (MA), from Addis Ababa University Faculty of Law specializing in areas of Human Rights in 2012. He was at Ministry of Justice both as a public prosecutor and Legal adviser at International Co-operation on Legal Affairs Directorate. During his stay he has acquired an extensive experience in Civil law, commercial law and criminal Law, prosecutions, Human Rights and International Law.